የከፍታው ዘመን ተጀመረ! (ሃፒ በርዝ ዴይ)

የከፍታው ዘመን ተጀመረ! (ሃፒ በርዝ ዴይ)
፡
ፒስ ነው ጋይስ?!
ቃሉን የማያጥፈው መንግስታችን "መጪው ዘመን የከፍታ ነው" ባለው መሰረት ከሰሞኑ ዶላሩን ደርሶ በማያቅበት ከፍታ ላይ ዱቅ አድርጎት "አላልኳችሁም!" ብሎናል፡፡እንግዲህ ከፍታችን እንዲህ እንዲህ ከሆነ በዚሁ ቢበቃን እና ወደ ለመድነው ሸለቆዋችን ብንመለስ ሳይሻለን አይቀርም!!
አንዲ ማኛማ "መንግስት ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ተርታ እየገሰገስኩ ነው" ያለውን አምና እራሷን ለማይቀረው የቅንጦት ኑሮ እያዘጋጀች ሁላ ነበር….ወይ ቅንጦት!? ጭራሽ መንግስት "ድንቡሎ ዶላር የለኝም! አዳሜ ከአሁን ወዲያ ከውጭ የምታመጭው መድሃኒት እና ምግብ ብቻ ነው!" ብሎን አረፈው….!!አምናና ካቻምና እኮ እንደጉድ እያደግን የነበረ መስሎኝ……. ?! ቆይ ግን ይሄን አይነት "መድሃኒት እና ምግብ ብቻ ግዙ!" አይነት መመሪያ "ኖርማል" ሀገር ላይ ያጋጥም ነበረ እንዴ ጋይስ?! እኔ በበኩሌ የኢኮኖሚ ማእቀብ ያልተጣለባቸው ሀገራት እንዲህ አይነት መመሪያ ሲያወጡ ስሰማ ትዝ አይለኝም!…እንደውም ይሄ መመሪያ የደርግን የ1977 መመሪያ ነው ያስታወሰኝ….ያኔ አገራችን በጦርነት እና በረሃብ ምናምን…. ብቻ የሆነ ጊዜ ላይ የለየላት ቦርኮ ሆና የደርግ መንግስት ከሰሞኑ መመሪያ ጋር ተመሳሳይ መመሪያ አውጥቶ ነበር…..ትዝ ይለኛል…ዶላር ለመቆጠብ ነዳጅ በኩፖን ሆነ፡ የቤት መኪና እሁድ መንዳት ተከለከለ….ወድ ጨርቃጨርቆች ከውጭ ማስመጣት ተከለከለ… ወዘተ… ፡፡ጋሽ መንጌ እራሳቸው አርአያ ለመሆን ሰማያዊውን ካኪ ፖሊስተራቸውን ለብሰው በቲቪ ከታዩ በኋላ መላው ሰራተኛ የሳቸውን ፈለግ እንዲከተል ቀጭን ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር……በእርግጥ አንዲ ማኛ ያኔ ልጅ የነበረች ቢሆንም የመንግስትን ትእዛዝ አክብራ "ሰማያዊ ካኪ ዳይፐር" አድርጋ በጀርባዋ ተንጋላ አጃዋን ስትጠጣ ትዝ ይላታል!.....እንግዲህ ከሰሞኑ ተመሳሳይ መመሪያ ከመንግስታችን እንጠብቃለን…..የዶላሩ ችስታነታችን ባስ ካለም ደግሞ መንግስት በሀገር ውስጥ የባህል መድሃኒት መፈወስ የሚችሉ በሽታዎችን መድሃኒት ማስመጣትም ከልክሎ "የቀበሪቾ ፋርማሲ" እና "የጤናአዳም ክሊኒክ" ቦሌ ሮድ ላይ እናይ ይሆናል!…..ለሽቶና ለዶድራንት ዶላር(ኤል ሲ) የሚጠይቅማ አለቀለት !"ዘመኑ የከፍታ በመሆኑ እነ ሊሊ እነ ቲቲ በአሪቲና በአደስ መዋብ ትችላላችሁ" ተብሏል…ሂሂሂ…. እስቲ እኛም ብቻ ሳንሆን እናንተም ዶላሩን ቆጠብ አድርጉት!…..ሻይ ቀጂና ቁልፍ ያዥ ጠሚውን ተከትሎ ወደ አሜሪካ ተንጋግቶ እየሄደ በአገረ አሜሪካ ዶላር በሚራጭባት አገር….አርፋ ጸጥ ብላ መቀመጥ ስትችል የጸጥታ ምክር ቤት ምናምን እያለች "ወጤን ቅመሱልኝ" ስትል የነበረች አገር እንደው ድንገት "ዱዲ ዶላር የለኝም !ምንም ከውጭ እንዳታስገቡ" ስትል ጎረቤትስ ምን ይላል….?!
ዶላር ተወደደ ብሎ የማሽላ ዋጋ የሚጨምር ነጋዴ ባለበት አገር ለመላው የችስታ ኮሚኒቲ(95 በመቶ የኢትዮጲያ ህዝብ) ኑሮው ከዚህ በላይ ሲኦል እንዳይሆንበትስ ምን ታስቧል?! እነ አቶ ዘመዴነህ "የብር ዋጋ ከዶላር አንጻር ዲቫሉዌት የተደረገው ኤክስፖርትን ኢንከሬጅ ኢምፖርትን ዲስከሬጅ ለማድረግ ነው አይዟችሁ!" ከማለት ውጭ ለእኛ ለአመዳሞቹ ምን መደረግ እንዳለበት መንግስትን ይመክሩት ይሆን?!....!ሁሌ እንደ ቡሄ ጨፋሪ መንግስትን ከማቆንጰለጳጰስ ወጥተው ደፈር ብለው መገሰጽስ ይችሉ ይሆን?!...አቶ እየሱስ ወርቅ የሚባሉ አንጋፋ ኢኮኖሚስት በቀደም እለት በቲቪ ስለ ኢትዮጲያ መጻኢ እድገት እና ኢኮኖሚ በሚደረግ ውይይት ላይ "እኔ በበኩሌ ጂቲፒ 2 እንደ ጂቲፒ 1 ስኬታማ ይሆናል ብዬ አላሰብም" ብለው "በእየሱስ!" ካስባሉኝ ወዲያ በሼባ ምሁሮቻችን ተስፋ ቆርጫለሁ…….ጋሼ የትኛው ጂቲፒ አንድ ነው የተሳካው…….?! አረ ኤዲያ!
እርግጠኛ ነኝ ይሄን ቢያነቡ "ታዲያ እንዳንተ ነጋ ጠባ መንግስትን ሳማርር ውየ ልደርልህ!?" የሚሉ ይመስለኛል፡፡በነገራችን ላይ እኔም አንዳንድ የመንግስታችን ስኬቶች ሳይታዩኝ ቀርተው አይደለም…….ለምሳሌ መንግስታችን በደርግ ሰአት ይሄ ሚስኪን ህዝብ 5 ኪሎ ስኳር ለመግዛት በቀበሌ ተሰልፎ በጸሃይ ሲንቃቃ ይውል የነበረውን ችግር ለማስወገድ በነበረው ቁርጠኝነት ዛሬ ስኳርን ከነጭራሹ በማጥፋት ችግሩን ከስር መሰረቱ አስወግዷል….ጎሽ የኔ አንበሳ…..!
የምር ለማነገር ግን አሁን አሁን እኔ የሚታየኝ ከፍታ የጥበት ብቻ ሆኗል..!በፊት ሀገሬ ሀገሬ ሲል የምታውቁት ህዝብ አሁን ጠቦ ጠቦ በየቀኑ አንደ አሜባ እራሱን እየከፋፈለ ይባዛ ይዟል…..በየቀኑ ቲቪ ስትከፍቱ የምታዩት" የእንትን ህዝብ እራሱን ለማስተዳደር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ አቀረበ!" ነው….ጉድ እኮ ነው…! ድሮ" እንትን ብሄር ከእንትን ብሄር እለያለሁ" አለ ነበር ወሬው ….አሁን ሰዉ ጠቦ ጠቦ ከአንድ ብሄር ውስጥም ጎጥ እየለየ መከፋፈል ይዟል…..እኛ ቤት እንኳን ከአንድ አባትና አንድ እናት የተወለድነው ልጆች መከፋፈያ ብናጣ "ሆስፒታል የተወለደ" እና "ቤት የተወለደ" ብለን በሁለት ጎራ ተከፍለን ዱቅ ብለናል….ለነገሩ ሆስፒታል ከተወለድነው ግሩፕ ውስጥም ከሰሞኑ "በምጥ የተወለደ" እና "በኦፕራሲዮን የተወለደ" ተብለን እንደገና ለሁለት ተከፍለን አንጃ ፈጥረናል…..ታዲያ እኛስ ምን እንማር!?...ለማንኛውም ሆስፒታል ከተለወድነው የእኛ ቤት ልጆች ውስጥ ዛሬ ጥቅምት ሁለት 19 መቶ …..ልክ በዚህ ሰአት ወደዚህ ዓለም የመጣሽው ውዷ እህቴ(ዘ ዋን ኤንድ ኦንሊ) ሜሪ ….ሃፒ በርዝዴይ ብያለው ….ባለሽበት ይመችሽ…. ….ስንት ስራ አቋርጬ ፌስ ቡክ አንቺን መልካም ልደት ልል ብገባ በወሬ ጥምድ አደረጉኝ እኮ!
ሌሎቻችሁ እንኳን….. ቅዳሜ ጥዋት እንገናኝ
እናም እስከዛው
ይመቻችሁ
- Home
- Wellness
- Theater
- Sports
- Shopping
- Religion
- Party
- Other
- Networking
- Music
- Literature
- Art
- Health
- Gardening
- Games
- Food
- Fitness
- Film
- Drinks
- Dance
- Crafts
- Causes