ማበድ ደጉ!

«ዘውድአለም ታደሰ»
ዳኒ የሰፈራችን ፅድት ያለ እብድ ነው። ቤተሰቦቹ ሃብታሞች ስለሆኑ ምንም ነገር አይቸግረውም። ልብሱም ንፁህ ነው። ያው አልፎ አልፎ የሚሰጠው የኪስ ገንዘብ ካልበቃው የሚግባባውን ሰው መጠየቁ አይቀርም። የሰፈሩም ሰው ስለሚወደው አይጨክንበትም።
ከዚህ በተረፈ ግን ዳኒ ጀንተል ያለ እብድ ነው። ለምን እንዳበደ ለምን እውቅ ሃኪሞች ጋር ሄዶ ሊፈወስ እንዳልቻለ የሚያውቅ የለም። ዛሬ ሰብሰብ ብለን ቡና የምንጠጣባት ቤት ቁጭ ብለን ነበር። ዳኒም ፈንጠር ብሎ በሩ ጋር ተቀምጧል። ድንገት ዳኒን የማያውቅ አንድ ነጭናጫ ሰውዬ መጥቶ አጠገቡ ተቀመጠና ቡና አዘዘ። ዳኒ የሆነ ነገር እንደሚለው ገምቼ የሚያወሩትን መከታተል ጀመርኩ ...
ዳኒ ሰውየውን ዞር ብሎ በጥርጣሬ ገላመጠው። ሰውየውም መልሶ ገላመጠው። ዳኒ ፈራ መሰለኝ ዞሮ ፈገግ አለ። ሰውዬውም ፈገግ አለና ጨዋታ ለመጀመር ያህል «ዘንድሮ በቃ ቤት ኪራይ ጣራ ነካ አይደል?» አለው።
ዳኒ አንገቱን ነቅንቆ «ነካ? ዘንድሮ ምን አናጢ አለ? ሁሉም ወንበዴ ሆኗልኮ» አለው።
ሰውየው ግራ ተጋብቶ «የምን አናጢ?» ሲለው ዳኒ ኮስተር ብሎ
«አናጢ አታውቅም? እነዚህ መዶሻ ይዘው ሚዞሩት ናቸዋ! ጣሪያውን ዝቅ አርገው ስለሚሰሩት እኮ ነው ኪራዩ ጣሪያ የነካው» ሲለው ሰውየው የብስጭት ሳቅ ስቆ
«አንተ ኮንዶሚኒየም ደርሶሃል መሰለኝ ትቀልዳለህ» አለው። ዳኒ ቡናውን ፉት ብሎ ዝም አለ።
ሰውየው ግን ዝም አላለም። «ኑሮ ተወዷል። ሁሉ ነገር እያሻቀበ ነው። አዲሳባ ላይ መኖር አልተቻለም» ሲለው ዳኒ አሁንም ቡናውን ፉት ብሎ
«ታዲያ መኖር ካልቻልክ እንዴት ኖርክ?» አለው።
«ሰውዬ አረ ቀልዱን አቁም። ልማታዊ ባለሃብት ነህ እንዴ?» አለው ከልቡ ተበሳጭቶ
«አዎ! ሃብታም ነኝ መሰለኝ።» አለ ዳኒ
«አረ ....ለዛ ነዋ። ለመሆኑ ምን እየሰራህ ነው?»
«አሁን?»
«አዎ»
«አሁን?»
«አዎ»
«ቡና እየጣሁ ነዋ»
ሰውየው በዳኒ ሁኔታ ግራ ተጋብቶ። «አይ ለመኖር ምን እየሰራህ ነው ማለቴ ነው?»
«ለመኖርማ እተነፍሳለሁ። እቅማለሁ። ቡና እጠጣለሁ»
«አይ ጥሩ ነው።» አለ ሰውዬው።
ጥቂት ፀጥታ ሰፈነ። ሰውየውም የቀረበለትን ቡና ፉት ብሎ ዳኒን በቆረጣ ይገረምመው ጀመር።
«አንተስ ለመኖር ምን ትሰራለህ?» አለው ዳኒ
«ጉምሩክ ነው ምሰራው?»
«ኦህ ጥሩ ስራ ነው። የራስህን ከፍተህ ነው?» ሲለው ሰውየው ትን እስኪለው ስቆ «አረ ተቀጥሬ ነው»
«ደሞዝህ ስንት ነው?»
«አራት ሺ ብር»
«በቀን ነው?»
«ሃሃሃሃ አረ በወር ነው»
«በወር ስንት ቀን?»
ሰውየው በዳኒ ጥያቄ ተገርሞ «በወር አንድ ቀን ነዋ»
«ታዲያ በወር አንድ ቀን ከተከፈለህ ለምንድነው ሰላሳ ቀን ምትሰራው?»
ሰውየው አሁን ትእግስቱን መቆጣጠር አልቻለም። «ሰውዬ በድህነቴ ለምን ታላግጣለህ? ደሃ ዘመድ የለህም እንዴ?» ሲለው ዳኒ ደንገጥ ብሎ
«አረ አለኝ። አክስቴ ደሃ ነች። ሁሌም ብር ስጪኝ ስላት የለኝም ነው ምትለኝ» አለው።
«አንተ እንዴት በዚህ እድሜህ ካክስትህ ብር ትጠይቃለህ?» ሲለው ዳኒ ፈጠን ብሎ «አይ እሷን ብቻ አይደለም ምጠይቀው። ሁሉንም ነው ምጠይቀው»
«ለምንድን ነው ሰውን ገንዘብ ምትጠይቀው?»
«እና ከሰው ሌላ ማንን ልጠይቅ?»
«አይ ሰውን ገንዘብ ከመለመን እግዜርን መለመን ይሻላል»
«እግዜር ብዙ ጠያቂ አለው። ላለማስቸገር ነው» ብሎ ቡናውን ፉት አርጎ አስቀመጠ።
ሰውየው ከኪሱ የቡናውን ሂሳብ እያወጣ «ለማንኛውም ስለተዋወቅን ደስ ብሎኛል» አለው ወደዳኒ ዞሮ
«መቼ ተዋወቅን?» አለ ዳኒ
«ውይ ለካ አልተዋወቅንም ሃብታሙ እባላለሁ» ብሎ እጁን ዘረጋ
«በወር አንድ ቀን እየተከፈለህ ሃብታሙ?» አለና ጨበጠው።
«እንገናኛለን» አለ ሰውዬው እየተነሳ
«የት?» አለ ዳኒ
ሰውየው ፈገግ ብሎ «እዚሁ ነዋ»
«መች?»
«ነገ መምጣቴ አይቀርም»
«ስንት ሰአት?»
ሰውየው ግራ ተጋብቶ «ልክ በዚህ ሰአት»
«አሁን ስንት ሰአት ነው?» አለ ዳኒ
«አሁን ሰባት ተኩል ነው»
«አይ ሰባት ተኩል አይመቸኝም» :)
- Home
- Wellness
- Theater
- Sports
- Shopping
- Religion
- Party
- Other
- Networking
- Music
- Literature
- Art
- Health
- Gardening
- Games
- Food
- Fitness
- Film
- Drinks
- Dance
- Crafts
- Causes