አይኔን በሌላ ሰው አይን ሳየው!

0
0

(አሌክስ አብርሃም)

ፍቅረኛየ በየቀኑ እንዲህ ትለኛለች
“ አብርሽ ‹የ› ” በቃ ‹ የ› ከጨመረች ጥያቄዋ ምን እንደሆነ አውቀዋለሁ …ቢሆንም እንደአዲስ ነገር ለመስማት 
“ወይየ” እላለሁ
“በናትህ ልጅ እንውለድ ” የሄው አላልኳችሁም ..አቤት ልጅ ስትወድ !
“የኔ ማር ልጅ ምን ይሰራልሻል ?”
“ልጅ እኮ በቃ…ምን ልበልህ …በቃ …..” ቃል ያጥራታል ትንፋሽ ሁሉ ያጥራታል የራሷን ጡቶች ጥብቅ አድርጋ አቅፋ አይኖቿን አንዴ ወደላይ አንዴ ….እያደረገች በቃ ስርቅርቅ ትላለች ….“ ልጅ እኮ ሲስቅ አስበው… የሆነ ሁለት ጥርሶች ብቻ ያበቀለ ኬክ የሆነ ልጅ (ኬክ ትወዳለች) …የሆነ ልጋጉ የሚዝረበረብ ቆንጅየ ልጅ ትንንሽ እጆቹ ሲወራጩ እጁ ፊትህ ላይ ሲያርፍ ….” በደስታ ታብዳለች ከዛ የሶፋ ትራስ አንስታ ታቅፍና “ አስበው ትንሽየ ንፁህ ቲሸርት የለበሰ ሙጥቅላ ንፁህ ፍጥረት አንተ ስታቅፈው .. ” ብላ ትራሱን ታቀብለኛለች አይኖቿን ጨፍና በራሷ ምኞት ትፈነድቃለች …ትራሱን ወደጎን ወርወር አድርጌ ስቀመጥ ልጁን የወረወርኩት ይመስል ትቆጣለች።

“ ልጅ ሲስቅ ደስ ይላል ግን እስኪ ሲያለቅስ አስቢው …ሌሊት ድብን ያለ እንቅልፍ ላይ ሁነሽ እንደሳይነር አፉን ሲከፍተው ኛአአአአአአአአአአአአአአአአአአአአአአአ ሲል ብታባብይው ዝም አልልም ሲል … ደግሞ ሲጫወት ብቻ ሳይሆን ሲታመምም አስቢ እንደተቀቀለ ፓስታ የተጥመለመለ ልጅ ይዘሽ በየሆስፒታሉ ስትዞሪ አስቢ …የምትወልጅው እኮ ሁልጊዜ ፒንክ እያለበሽ ከጧት እስከማታ ዘንጦ የሚውል አሻንጉሊት አይደለም ….አሁን ሱሪ ቀይረሽለት ቲሸርቱን ልታለብሽው ስትታገይ ከስር .በርጨጭጭጭጭጭጭ የሚል ድምፅ ያውም ቤቱን ከሚያጥነገንግ ሽታ ጋር ….”

“አያደርግም የኔ ልጅ አይገርምህም ” ትልና ገና ላልተወለደው ልጅ ትከራከራለች።

እኔም በተቻለኝ ሁሉ ማጥላላቴን እቀጥላለሁ …“ በዛ ላይ ዋክ መውጣት የለ መዘነጥ የለ (ዋክ እና መዘነጥ ነፍሷ ነው ) በዚያ ላይ ልጁ አንድ አመት እስከሚሆነው ሳያቋርጥ የሚያለቅስ ልጅ ሊሆን ይችላል በቃ ጡጦ ለመጥባት ብቻ ዝም የሚል ክፍታፍ ልጅ ”

“የኔ ልጅማ ጡጦ አይጠባም ጡቴ የት ሂዶበት ” ትልና ጡቷን ታሳየኛለች ጡቷ በጣም ነው የሚያምረው ልጅ የተባለው ነገር እነዚህ ውብ ጡቶቿ ላይ እንደመዥገር ሲጣበቅባቸው ሳስበው ገና ቀፈፈኝ !

“እንዴ ጡትሽነማ አይነካትም ….እኔስ ” እላታለሁ ላቅፋት እየሞከርኩ

“አንተማ ጡጦ ትጠባለህ ” ትላለች ልክ እንዳልገባት ሳቋ ግን ከንፈሯ ጥግ ደርሷል ያስታውቃል !

“ልጅ ማለት የወላጆች አሻንጉሊት አይደለም አይምሮን ከልጅ አስደሳች ገፅታ ጀርባ ላለው መስዋትነትም ማዘጋጀት ያስፈልጋል ”
“አትፈላሰፍ ” ትለኛለች።

እንግዲህ እንዲህ ስንነዛነዝ አንድ አመት ሆነን ….ጭራሽ እንደውም “ አንተ አላማ የለህም አባት የመሆን ሞራሉም ፍላጎቱም አልተፈጠረብህም በቃ መተኛት መነሳት መተኛት መነሳት መሳሳም ካፌ ለካፌ መዞር ….መተኛት መነሳት ምንድነው እድሜን ሲጃጃሉ ማሳለፍ ” ብላ ተለየችኝ !

በቃ ጨክና ሄደች ብለምን ባስለምን አይንህን እንዳላይ ብላ ቆረጠች ….ከሌላ አንድ አመት በኋላ እዚህ ወሎ ሰፈር ጋር አየኋት የደረሰች እርጉዝ ሁና! በእርግጥ ቀንቸ ነበር …በማርገዟ ሳይሆን ለማርገዝ የተደረገው ነገር ሁሉ ሌላ ወንድ ጋር መደረጉን እያሰብኩ ……..

ድብር እንዳለኝ እቤቴ ገብቸ ተኛሁ …ወይ ጉድ ሰውለማርገዝ እንዲህ …ግን ምናለ እሽ ብላት ኖሮ ታፈቅረኝ ነበር በዛ ላይ እኔን ብላ እንጅ መልክ ቢባል ሳይሰስት ያደላት በዛ ላይ የናጠጡ ሃብታም ቤተሰቦች ያሏት ነበረች ምናለ ብታረግዝ ኖሮ ቆጨኝ …ወዲያው ከጎረቤት ውሻ ሲጮህ ሰማሁ “ ውውው ” የውሻውን ጩኸት ተከትሎ የሚፍለቀለቅ የህፃን ሳቅ “ ውውው” ከዛ የህፃን ሳቅ …ኮንዶሚኒየም ሶስተኛ ፎቅ ላይ ውሻ እንዴት ሊገኝ ቻለ ብየ ገርሞኝ በሬን ከፍቸ ወጣሁ። …..

ጎረቤቴ አንድ አመት የሆናት ህፃን ልጁን እያጫወተ ነበር “ ውው ” ይላታል እንደውሻ …. ከትከት ብላ ትስቃለች ልጅቱ … ከዛ ልክ እንደአጥንት አንጠልጥሏት ወደአንዱ ጥግ ጀፍ ጀፍ እያለ ይሮጣል…. ወይ አባት መሆን ከዛ እዛጋ አስቀምጧት “ውው ” …ይሄ ሰውየ ፊቱ የመማይፈታ ኮስታራ ሰው ነው ይሄው እንደውሻ ለልጁ ይጮሃል …..

ታዲያ ወደቤቴ ስመለስ እንዲህ አልኩ “ ተመስገን አምላኬ ምናልባትም እኔ ብወልድ እንጅብ እጮኽ ነበር ይሆናል ” የፍቅረኛየ ባል እንደውሻ እየጮኸ ፍቅረኛየም እንደላም እንደዶሮ እንደውሻ እየጮኸች ልጃቸውን ሲያጫውቱ ታየኝ እና ሳቄ መጣ ….ውስጠኛው አይምሮየ ግን “ ባክህ ራስህን አትሸውድ እንዲህ ሬሳ የወጣበት ቤት ከሚመስል ጭርታ ከልጅ ጋር እንደውሻ መጮህ በስንት ጠአሙ ” ይለኛል።

Search
Categories
Read More
Uncategorized
1964
The chief army commander General Derese Dubale visiting the 4th national first-rank army service....
By Seller 2017-11-14 07:31:18 0 0
Uncategorized
ተዋናይ ዳንኤል ተገኝ ከ80 በላይ ለሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች መሉ አልባሳቱን ለገሰ
ETHIOPIA – ተዋናይ ዳንኤል ተገኝ ከ80 በላይ ለሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች መሉ አልባሳቱን ለገሰ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ለአገር እና ለሕዝብ...
By binid 2017-11-12 15:07:32 0 0
Uncategorized
በህይወት እስካለህ ልትሳሳት ፣ ልትወድቅ ትቸላለህ
በህይወት እስካለህ ልትሳሳት ፣ ልትወድቅ ትቸላለህ ፣ ሰዎች ላይቀበሉህ ይችላሉ ፣ ወይም ሀሳብህን ላይረዱህ ፣ ቦታ ላይሰጡህ ይችላሉ ፣ በእጅህ ላይ ያለው...
By Dawitda 2017-11-13 09:59:25 0 0
Uncategorized
አንዳንድ ቅዳሜዎች
አንዳንድ ቅዳሜዎች፡በጣም ጠፋሁ አይደል!!; አይ ኖው…. አይ ኖው….አይ ሚስ ዩ ቱ ጋይስ፡፡ያው መጥፋቴ የቢዴና ነገር ሆኖብኝ...
By andualem 2017-11-12 15:15:06 0 0
Uncategorized
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የተከታታይ ትምህርት መርሃ-ግብሮች ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ተባለ፡፡
ተከታታይ የትምህርት መርሃ-ግብር አያሌ ዜጐችን በማታ፣ በክረምትና በእረፍት ቀናት ተምረው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ማስቻሉ በጥናት...
By Seller 2017-11-15 07:31:38 0 0