‹‹በህልም የተፈጠረ መወስለት ከሐጢያት ይቆጠር ይሆን?››

‹‹በህልም የተፈጠረ መወስለት ከሐጢያት ይቆጠር ይሆን?››
(አሳዬ ደርቤ)
እንዴት ዋላችሁ ምዕመናን?
እኔ ባሳለፍነው ሌሊት ከስንት መንጠራራትና ማዛጋት በኋላ የወሰደኝ እንቅልፍ ያልሆነ ህልም ውስጥ አስገብቶ ሲያዳክረኝ ካደረ በኋላ እንዱንም ሳልቋጨው አስበርግጎ ስለለቀቀኝ ቀኔን ያሳለፍኩት በጸጸትና በንደት መሃከል ስወዛገብ ነው፡፡
ከሁሉ አስቀድሜ መናገር የምፈልገው ነገር… ስተውንበት ያደርኩት ህልም እናት አገራችን ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ ያላገናዘበና አንድ ታማኝ ባለትዳርን ያባለገ በመሆኑ በተባበረ ክንዳችሁ ብታወግዙት ቅር አይለኝም፡፡
በእውነቱ የልቤን ጥንካሬ የተረዳው ጋኒን ጊዜውን የኋሊት ጠምዝዞና ጭንቅላቴ ውስጥ ያለውን የጋብቻ ፋይል ሰርዞ… ከሰርጌ በፊት ወዳለው ዘመን በመመለስ ለትወናው ምቹ ሁኔታን ባይፈጥርልኝ ኖሮ ልሳሳት ባላቻልኩኝ ነበር፡፡ (ብሳሳት እንኳን እኔ አሳዬ ደርቤ ኮንዶሜን ደርቤ እንጂ…. Lol)
ወደ ህልሜ ላስገባችሁማ!
ሜክሲኮ አካባቢ ነው፡፡ (የህልም መቼቴን አዲስ አበባ ላይ ያደረገው ሰይጣን ሚስቴን የት እንዳደረሳት ‹‹እሱን ስትጸበል ታወራዋለህ!›› ብለን እንለፈው፡፡
እናላችሁ በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ሶሉን ያስቀየርኩትን ብቸኛ ‹ሹልቴክስ ጫማዬን› ከሚቀባልኝ ሊስትሮ ወንበር ላይ ተቀምጨ ይመስለኛል፡፡
ሊስትሮው ወደ ሰማይ ያንጋጠጠውን የጫማዬን ጫፍ በመዶሻ በመቀጥቀጥ መሬት ለማስነካት እየታገለ ‹‹መቼም ጋሼ ሂሳቡን ባግባቡ ብትመዘግበው ኖሮ ይህች ‹ጥሩንባ› መሰል ጫማ ከተገዛችበት ዋጋ ይልቅ የተቀባችበት ዋጋ በእጥፍ መብለጡ አይቀርም ነበር›› ይለኛል፡፡
ከዚያም በሊስትሮው ድፍረት በሽቄ ጫማዬን በማጥለቅና መሃል ቂጡን በካልቾ በመዛቅ ጠደፍ፣ ጠደፍ እያልኩኝ ስሄድ… መንገድ ላይ ከአንዲት አጭር ጉርድ ከለበሰች… ነዶ ጸጉሯን በማንጅራቷ አዙራ ያበጠ ጡቷ ላይ ከነሰነሰች… ብስል ፊት፣ መለሎ ቁመት፣ የጎመራ ከንፈር፣ ጉደኛ ‹ፖስቸር› ካላት ‹ምልዑና ደንቧሻ› ሴት ጋር እገጣጠማለሁ፡፡ (ምነው በሌላ መንገድ ሄጄ በሆነ!)
ልጂቱ እየቀረበችኝ በመጣች ቁጥር ኮስሞቲክስ አልባ ውበቷ አስገርሞኝ አፌን ከፍቼ ሳዘግም የሆነ ድንጋይ ያነቅፈኝና በአፍ-ጢሜ ልተከል ስል ለስላሳና ውብ ጭኗን ጨምድጄ ለጥቂት እተርፋለሁ፡፡
እናም እግሯን እንደጨመደድኩ ቀና ብዬ ስመለከታት ንጣትና ውበት ባንድ ላይ የታደለውን ጥርሷን አፍክታ ልክ እንደሚተዋወቅ ሰው ‹‹እኔ እኮ አላምንም!›› ትለኛለች፡፡
የት እንደማውቃት እያሰላሰልኩ እንዳለ ‹ጋኒኑ› በጆሮዬ ጠጋ ብሎ ‹‹የፌስቡክ ጓደኛህ እከሌ እኮ ናት›› ይልና ሊንኩን ያቀብለኛል፡፡
ከዚያም ‹‹ቤቲ ስዊት እንዳትሆኝ!›› ስላት እራሷ መሆኗን ጭንቅላቷን በመወዝወዝ ትነግረኛለች፡፡ (ስሟን ስለቀየርኩት ሰርች ማድረጉን ትታችሁ ተከታተሉኝ!)
እኔ ልሙትላችሁ የጋለበኝ ሰይጣን ከምኔው ከወደኩበት አስነስቶ፣ ከምኔው የባጥ የቆጡን አስወርቶ ለምሳ እንዳደረሰልኝ እሱ ይወቅ፡፡
‹‹ክላስ ነገር ይዘን ብንጫዎት ይሻል ይሆን?›› እላታለሁ፡፡
‹‹አይ ቤትህ ብንሄድ ይሻላል›› ትለኝና እግረ-መንገዷን የሸገር ልጅ አለመሆኗን ትነግረኛለች፡፡ (መቼም የሸገር ልጅ ብትሆን ኖሮ ላቀረብኩላት ጥያቄ ባለኮከብ ሆቴል እንጂ የተዝረከረከ ሳሎን አትመርጥም ነበር፡፡ (ሲጀመር የሸገር ሴቶች መኪናና ሱፐር ማርኬት መኖርህን ሳያጣሩ መቼ ወደገደለው ይገባሉ? በህልማቸው እንኳን ከእግረኛ ጋር የማይፎርሹ ጉዶች አይደሉ እንዴ?)
.
ትችቱን ትቼ ወደ ትዕይንቱ ስመለስ…. ቤትህ ውሰደኝ እንዳለችኝ የሆነ ታክሲ በአጠገቤ ሊያልፍ ሲል በፉጨት አስቆመዋለሁ፡፡ (በአፍላ የወጣትነት ዘመኔ ብዙ ጊዜ ሞክሬ ልለማመደው ያልቻልኩት ፉጨት እንዴት በህልሜ ሊከሰት እንደቻለ አልገባኝም፡፡)
አፏጭቼ ያስቆምኩት ታክሲ ውስጥ ልገባ ስል በገሃዱ ዓለም የምታስቸግሩኝ አንሶ በህልሜም ተከስታችሁ የተለመደ አበሻዊ ምቀኝነታችሁን ይፋ አደረጋችሁት፡፡
በሚገርም ሁኔታ እንደ ጉንዳን ተቀጣጥላችሁ ‹‹ስማ! እኛ እኮ እዚህ የተሰለፍነው ታክሲ እየጠበቅን እንጂ ጸሐይ እየሞቅን አይደለም›› ትሉኛላችሁ፡፡
‹‹እና ጸሀይ የሚያጠወልጋት ‹እንቡጥ አበባ› (እንዲሁም ቀዘባ) ይዤ እናንተ ጋር ተሰጥቼ ልዋል?›› በማለት ኮረዳዋን ታቅፌ ወደታክሲው ልገባ ስል አንባገነን መንግስታችሁ ላይ ልታሰሙት የሚገባውን ተቃውሞ አንድ ምስኪን ወንድማችሁ ላይ ታንጸባርቁት ጀመር፡፡ በዚህም የተነሳ ከህልሜ አልፎ እስካሁን ድረስ የዘለቀ ቅያሜየን በልቤ አኑሬ ጣኦቴን ከእናንተ ጋር ለማሰለፍ ተገደድኩኝ፡፡ ከዚያም ከሰልፉ መጨረሻ በመሄድ ከኮረዳዋ ጀርባ ላይ ተለጥፌ እንደ እርግብ አንገት የሚለሰልስ ማጅራቷን በስሱ ስስማት ‹‹አበስኩ ገበርኩ! አይ ስምንተኛው ሺ!›› አይነት ዝባዝንኬ እያወራችሁ ፋታ ታሳጡኛላችሁ፡፡ ይሄም ሆኖ ‹ይለይላችሁ› በማለት ከንፈሯን ለመጉረስ ስንጠራራ የሆነ እጅ ትከሻዬን ይዞ ወደ ኋላ ይስበኛል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጉብሏም ፊቷን አዙራና ከንፈሯን ገርበብ አድርጋ ልትስመኝ ስትል እሷንም ጠፍንጋችሁ በመያዝ ‹‹በአደባባይ'ማ እንዲህ አይነት ብልግና አይፈጸምም›› ትሏታላችሁ፡፡ እናም በዚህ ድርጊታችሁ ኮረዳዋ ተበሳጭታ ፊት ለፊት ወደሚታየኝ ሆቴል በጣቷ እያመለከተች ‹‹ና ማርዬ እዚያ ሆቴል እንሂድና ክላስ እንያዝ›› በማለት በሎጋ ጣቷ እየሳበች ይዛኝ ትሄዳለች፡፡
ከዚያም ሆቴሉ ውስጥ ወዙ ችፍ ችፍ ያለ ዝልዝል ጥብስ በእኔ ሂሳብ ከጋበዝኳት በኋላ በዋሌቴ ከያዝኩት በርካታ ገንዘብ መሃከል ጥቂቱን ቀንሼ በማውጣት የምሳ ሂሳቡን ከአልጋው ጋር በመደመር ከፍዬ ወደተያዘልን ክላስ ልንገባ ስንል አንዲት አስተናጋጅ ወደ እኔ ትመጣና በድጋሜ እንዲከፍል ትጠይቀኛለች፡፡
‹‹ከፈልኩ እኮ›› ብያት ልሄድ ስል ኮሌታዬን ጨምድዳ ‹‹በፍጹም አልከፈልክም›› ብላ ድርቅ ስትል… ኮረዳዋ እየተቅለሰለሰች ‹‹እባክህን ውዴ ፍቅር የምንሰራበትን ሰዓት በክርክር አታሳልፈው›› እያለች ልታግባባኝ ብትሞክርም የገሃዱ ዓለም ባህሪዬን ከስቼ ‹‹ቆሜ ነው ሞቼ ሁለተኛ የምከፍለው›› እያልኩ ስንገታገት አስተናጋጇ ትከሻዬን እየወዘወዘች ‹‹ሳትከፍልማ አትሄዳትም›› ትለኛች፡፡
እናም ውዝዋዜውና ንቅናቄው እየበረታ ሲመጣ የኮረዳዋ ፊት እየከሰመ፣ የሚስቴ ፊት እየለመለመ ይታየኝ ጀመር፡፡
ነገርዮው እየተከሰተ ያለው በህልም መሆኑ ሲገባኝም ከመባተቴ በፊት ከፍለ-ሐገር እያለሁ በህልሜ ስጠቀምበት የነበረውን የመንሳፈፍ ጥበብ እውን በማድረግ እንደ Spider man ኮረዳዋን አንጠልጥዬ ወደ አልጋ ቤቱ ይዣት ለመሄድ ተፍገመገምኩኝ፡፡ ሆኖም ግን አዲስ አበባ ላይ የሚካሄድ ህልማዊ ጉዞ በሰልፍ እንጂ በመንሳፈፍ የሚታጀብ ባለመሆኑ ሳይሳካልኝ ቀረ፡፡
ይሄም ሆኖ በቅጽበት ውስጥ ከወንደላጤነት ወደ ልጅ አባትነት ላለመዛወር ህልሜ ውስጥ ለመቆየት መፍጨርጨሬን አልተውኩም፡፡ ከዝልዝል ጥብስ ወደ ሽሮ ፈሰስ ላለመመለስ በከባዱ ተስለመለምኩኝ፡፡ ሙሉ በሙሉ ከመንቃቴ በፊትም ያለኝን ገንዘብ በሞላ ከእነ ዋሌቱ ለአስተናጋጇ ልሰጣትና ሸሚዜን ላስለቅቃት ተጣደፍኩኝ፡፡
ሆኖም ግን በአስተናጋጇ ተመስላ እጅ ከፍንጅ የያዘችኝ ሚስቴ ልትለቀኝ አልቻለችም፡፡ እናም የቲሸርቴ ኮሌታ ስፌቱ እስኪተረተር ድረስ ጨምድዳ እየሰባች ልታባትተኝ ስትታገል በእንቅልፍ ልብ ውስጥ ሆኜ ‹‹ምን ሆንሽ?›› የሚል ጥያቄ አወጣሁኝ፡፡
‹‹ሽሮው ሳይቀዘቅዝ ተነስና ቁርስህን ብላ እንጂ!›› ስትለኝ ‹‹በልቻለሁ ማለት አማርኛ አይደለም እንዴ? አንቺ ሴትዮ ግን የእንቅልፍ ክቡርነት የሚገባሽ መቼ ነው?›› ብያት ከአልጋዬ ላይ ተስፈንጥሬ በመነሳት ወደ ውጭ ወጣሁኝ፡፡
ከዚያም ስሟንና ብልግናዋን ያልረሳሁላትን ያችን አሳሳች ዉብ ኮረዳ በሚሴጅ ልክ-ልኳን ልነግራት ስሟን ፌስቡክ ላይ አስፍሬ ‹ሰርች› አደርጋት ጀመር፡፡

- Home
- Wellness
- Theater
- Sports
- Shopping
- Religion
- Party
- Other
- Networking
- Music
- Literature
- Art
- Health
- Gardening
- Games
- Food
- Fitness
- Film
- Drinks
- Dance
- Crafts
- Causes