‹‹ስጋን ማመን አርዶ ነው!››

0
0

‹‹ስጋን ማመን አርዶ ነው!››
(አሳዬ ደርቤ)
‹‹ምሳዬን የት ልብላ?›› የሚል አጀንዳ ይዤ ስብሰባ ገባሁኝ፡፡
ኪሴ ‹አርከበ-ቤት› የሚል ሃሳብ አመነጨ፡፡
ከርሴ ደግሞ ‹ሉካንዳ-ቤት አድርገው› እያለ ወሰወሰኝ፡፡ እናም በርካታ ጊዜ ከወሰደ ስብሰባ በኋላ አቅሜንና አምሮቴን ያገናዘበ ውሳኔ በማሳለፍ ወደ ሉካንዳ-ቤት ስገባ ትልልቅ ጨጓራ ያላቸው ሰዎች ይሄን የበሬ ስጋ በጥሬውና በጥብስ መልክ ሲበሉ በማየቴ… ‹ሰላሳ ሊትር/ሰከንድ›› በሆነ ልኬት አምሮት የወለደው ምራቅ አፌ ውስጥ ይመነጭ ያዘ፡፡ መሃል አናቴም ላይ ስጋ ሊያበስል የሚችል እንፍላሎት ሲግተለተል ተሰማኝ፡፡
ሉካንዳ ቤቱን የሞሉትን ተመጋቢዎች ስጋ ሳይሆን ሙስና ሲበሉ ያገኘኋቸው ይመስል በጥላቻና በንቄት ስሜት እያየኋቸው ከአንዱ ጥግ ላይ አረፍ ከማለቴ የሆነ አስተናጋጅ እየተክለፈለፈ መጥቶ ‹‹ምን ልታዘዝ›› ሲለኝ… ከስንት ስሌት በኋላ ‹‹የፈጀውን ይፍጅ›› ብዬ ልበላው የወሰንኩትን የምግብ ስም በመጥራት‹‹ምላስ-ሰንበር›› አልኩት፡፡ 
‹‹የሚጠጣስ ምን ይምጣልህ?›› አለኝ፡፡
‹‹ውሃ አድርገው›› አልኩት፡፡
‹‹አኳ-ሴፍ ይሁን ወይስ?››
‹‹ቧንቧ-ሴፍ ይሁን››
‹‹የቧንቧ ውሃ የለም››
‹‹በቃ መረቅ አምጣልኝ›› ስለው በእጁ በያዘው የኒኬል ትሪ ግንባሬን ማለት እያማረው ‹‹ለቅቅል እንጂ ለምላስ ሰንበር መረቅ አይሰጥም›› ብሎኝ እየተማነቀረ ሄደ፡፡ (ባዘዝኩት ምግብ የበታችነት ስሜት ሊሰማኝ ሲጀምር ከዋጋውን ዝቅተኝነት ይልቅ በውስጡ የያዘውን የምግብ ይዘት በማስታወስ ለመጽናናት ሞከርኩኝ፡፡)
.
ሆቴል ውስጥ ስገባ እጅግ የሚያበሳጨኝ ነገር ‹‹የሚጠጣስ ምን ይምጣልህ?›› የሚል አድርቅ ጥያቄ ነው፡፡ እውነት እላችኋለሁ ከዚህ ጥያቄ ይልቅ ቢለዋ ቢሰነዘርብኝ እመርጣለሁ፡፡
አንዳንድ ምግብ ቤቶች ጋር ስትሄዱማ የሚጠጣ ነገር የሌለበት ባዶ ምግብ ብቻውን አያቀርቡላችሁም፡፡ ‹‹ምነው?›› ስትሏቸው ‹የቤቱ ህግ ነው› ይሏችኋል፡፡ እናም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ በቤንዚን ዋጋ የሚሸጥ ውሃ ከጠጣችሁ በኋላ የመበሳጨት እንጂ የእርካታ ስሜት ስለማይሰማችሁ ሌላ ነገር ብትጠጡ ጥሩ ነው፡፡
ግን እንደው ምላስ-ሰንበሩ እስኪመጣ ድረስ በውሃ ጥም ውስጥ ሆነን ስለ ውሃ ስናወራ…. የቧንቧው እየጠፋ ባለበት ሰዓት የኮዳው እየተስፋፋ መምጣቱ ከጀርባው ሴራ ያለበት አይመስላችሁም፡፡ 
አስቡት እስኪ የከተማው ህብረተሰብ በውሃ ፈንታ የቧንቧ ተጠቃሚ በሆነበት ሰዓት… መንግስት የውሃ ወረፋ አውጥቶ በፕሮግራም መጠማትንና በፕሮግራም መቅዳትን እያስተማረ ባለበት ሰዓት… ከአዲስ አበባ ጀርባ ያወጡትን ውሃ አሽገው በቤንዚን ዋጋ የሚሸጡ የውሃ ፋብሪካዎች በብዛትም ሆነ በአቅርቦት ተደራሽነታቸው እየሰፋ ይገኛል፡፡
እናም ይሄን ስታስቡ ‹‹መስታወት ጠጋኝ ስትሆን መስታወት ሰባሪ ማሰማራትህን አትዘንጋ›› እንደሚባለው… ከውሃ ቢዝነሱ ጀርባም ታንከር የሚታሸግላቸውና ታሪፍ የማይሰራላቸው አንዳንድ ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንት በባለሐብትነት ወይም ደግሞ በጥቅም ተከፋይነት ያሉበት አይመስላችሁም? 
.
ያዘዝኩትን ‹ምላስ-ሰንበር› አስተናጋጁ ከአፍንጫው ራቅ አድርጎና በሰርቪስ ላይ ገልብጦ በማምጣት ከፊቴ አስቀምጦልኝ ሲመለስ በአምሮቴ ፈንታ ስጋቴ ትሪው ላይ ተቀመጠ፡፡ እናም የመጣልኝን የጨጓራ ክምር እየጸለይኩ ሳይሆን እየሸከኩ አስተውለው ጀመር፡፡
ምን ላድርግ? አሁን አሁን አንዳንድ ሉካንዳ ቤቶች ከእጃቸው የገባውን ነገር ሁሉ ማረድ ጀምረዋል አሉ፡፡ እናም አንድ እንስሳ በማሞስካቱ ሳይሆን በእንስሳነቱ በሚታረድበት አገር ላይ እያሰቡ እንጂ እየተስገበገቡ መብላት እንዴት ይቻላል?
ሚስቴም ብትሆን በባለፈው ‹የጅብ ስጋ የሚሸጡ ሰዎች› መያዛቸውን ከሰማች በኋላ ‹‹ስጋን ማመን አርዶ ነው›› በማለት ዘወትር የምትመገበው ‹ሰላሱት› ሁኗል፡፡ ስጋ የሚያስገዛ ነገር ካጋጠማትም በኪሎ የምትገዛው ጥሩ ስጋ ከሰቀለው ሳይሆን ሸኮና ካንጠለጠለው ሉካንዳ-ቤት በመሄድ ነው፡፡
ምላስ-ሰንበሩን ሰረቅ አድርጌ አየሁት፡፡ ብዛቱ የአውሬ እንጂ የበሬ አይመስልም፡፡ 
እናም ስጋው ያሳደረብኝን ስጋት ለመቀነስ በማሰብ… አስተናጋጁን በምልክት ጠራሁትና ‹‹ቅመስልኝ›› ከማለት ይልቅ አንዳች የሚያክል ጉርሻ ጠቅልዬ ወደ አፉ ተተኮስኩኝ፡፡
ይሁንና አስተናጋጁ ላንቃውን በርግዶ ጉርሻዬን እንደ መቅለብ አፉን በመዳፉ ሸፍኖ ‹‹ስጋ ከበላሁ ጥርሴን ያመኛል›› በማለት ሊከላከለኝ ሲሞክር ‹‹ምንም አያደርግህም ስልህ… አፈር ስሆን፣ ስቀበርልህ እያልኩህ….›› ወዘተረፈ በማለት ቆሜ ብለማመጠውም በጄ አላለኝም፡፡
ይልቅስ ‹‹የጥርስ ህመም አለብኝ ማለት አማርኛ አይደለም እንዴ?›› በማለት ጉርሻዬን ገፍቶትና ጥርጣሬዬን አግዝፎት ሄዴ፡፡
ይሄም ሆኖ ግን… አላፊ አግዳሚውን ‹‹እንብላ›› እያልኩኝ… ‹‹ሰንበሬን›› እያዳመጥኩኝ…. ‹‹የእናትና የስጋ መጥፎ የለውም›› እያልኩኝ ግንባሬን ክስክሼ ሳልበላው አልቀረሁም፡፡

ፍለጋ
Categories
Read More
Uncategorized
ዘውዲቱ ሆስፒታል 5 የኩላሊት እጥበት መስጫ መሳሪያዎችን በወቅቱ አለመግዛቱ ችግር ፈጥሮብናል
ዘውዲቱ ሆስፒታል 5 የኩላሊት እጥበት መስጫ መሳሪያዎችን በወቅቱ አለመግዛቱ ችግር ፈጥሮብናል-ታካሚዎች ዘውዲቱ ሆስፒታል ከአንድ ዓመት በፊት ለአምስት...
By binid 2017-11-26 06:52:11 0 0
Uncategorized
_ከምድር ሁሉ ሃብታሙ ስፍራ……..መቃብር
__ከምድር ሁሉ ሃብታሙ ስፍራ……..መቃብር “The graveyard is the richest place on earth,...
By Seller 2017-12-01 08:05:09 0 0
Other
HÀNG BÃI NHẬT: Xe Nâng Điện KOMATSU FB10-12 Bảo hành dài hạn, Giao hàng tận nơi
Bạn đang tìm kiếm một chiếc xe nâng điện mạnh mẽ, tiết kiệm, linh hoạt và an...
By xenangaz 2025-04-17 07:38:45 0 0
Uncategorized
ሀገራዊ ዕብደት
(ዳንኤል ክብረት) ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ በቤታችን ደኅና መጥፋቱ ነወይ የሚል የበገና ዘለሰኛ አለ፡፡ አሁን ያለችውን ሀገራችንን ቀድሞ ያየ...
By binid 2017-11-25 13:24:18 0 0
Uncategorized
አስገራሚ ቃለ ምልልስ -ሙጋቤ
”መቼም ሙጋቤ መልካም ሰው ነው” ይላል- መንግስቱ ሃይለማርያም የክፉ ቀን ደራሹን ማመስገን ሲጀምር።በርግጥ የሙጋቤን መልካምነት...
By binid 2017-11-26 06:36:34 0 0