‹‹ እፎፎፎፎይ አሉ እቴጌ ጣይቱ››

0
0

አሌክስ አብርሃም
‹‹ እፎፎፎፎይ አሉ እቴጌ ጣይቱ››
(ከድድ አድማስ ኋላ)

እዚህ አራዳ ህንፃ የሚባለው አንደኛ ፎቅ የሚገኝ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጨ ቁልቁል እመለከታለሁ …. እየተመለከትኩ ከዚህ በፊት ስለፈረሰው ትዳሬ አስባለሁ ….እንኳን የከበረውን ትዳር ለመተንተን ራሳቸውን ችለው መቆም የማይችሉ መደዴዎችን የትዳር ትንታኔ ስሰማ መኖሬ ነው ስለትዳር የተጣመመ እይታ እንዲኖረኝ ያደረገው እያልኩ እቆላጫለሁ ! ትዳር በማንም አፉን በየመንደሩ መክፈት በለመደ ቡሃቃ አፍ ሲተነተን ያቅለሸልሸኛል !

ትዳር መንፈስ ነው ለዛም ነው የስጋ እንቶፈንቶን መቁጠር ሲጀምር ጎጆ የሚያዘመው ….. እንደኔ እንደኔ ከዘልዛላ አብሮነት ‹‹ፍቅር›› ከሚመስልም መጓተት የፈረሰ ትዳር የተሻለ ክብር ይገባዋል እላለሁ !የግድ ጎትተው ፍቅረኝነት እና ትዳር አንድ ነው ልዩ ነቱ ያው ህጋዊ አለመሆኑ ምናምን ሲሉ መጀመሪያ አእምሮየ ውስጥ የሚመጣው ‹‹ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ነሽ ይሏታል›› ይሉት ፈሊጥ ነው !! አይቻለሁ በዚህ ፈሊጥ ስታመልጥ ፍልጣቸውን መዘው ዘራፍ ሲሉ ! ፍልጥም ፈሊጥም እጣ ፋንታን አይገዛም እንጅ!!


ለዛም ነው ‹‹በፍቅር ያሳለፍነው ጊዜ እነዛ ጣፋጭ ጊዜያት ዋው ምናምን›› እያሉ ከሚያላዝኑብኝ የድሮ ፍቅረኛዎቸ በላይ ተፋተንም ቢሆን በትዳር አብሪያት ለነበርኩት ሴት ልቤ የሚደነግጠው ! የሆነ ማንትስ የሚባል ፈላስፋ ትዛዝ አይደለማ ትዳር ! አምናለሁ መለኮታዊ እስትንፋስ እንዳለበት …አየህ ፈጣሪህን በብዙ ነገር እንደማትታዘዘው ሁሉ በዚህም እሱን እምቢ ማለት በትዳር መፍረስ ውስጥ ዋናው መዘዝ ነው እላለሁ ! እውነት ነው ሰዎች በተለያየ ምክንያት ላይስማሙ ይችላሉ (ሰበቡ ብዙ ነው) ….ትዳራቸው ሊፈርስም ይችላል ….ግን የማይፈርስ እውነት ውስጥህ አለ … ትዳር የሚባለው መለኮታዊ ጉዳይ አንተ ራስህ ስርአት ባይኖርህ እንኳን አንዳች መለኮታዊ ጥበቃ ያለው ክቡር አብሮነት ነው !!

ለምን ይመስልሃል ፍቅረኞች ሲለያዩ ማንም የማይደንቀው …እ ተለያዩ እንዴ ብሎ ዝም ! እንደውም ‹‹ለበጎ ነው›› ይልሃል ! ባለትዳሮች ተፋቱ ሲባል ግን አግብቶ የማያውቀው ሰው ልብ እንኳን ሲደነግጥ ትታዘባለህ(ምን አስደነገጠው እስቲ) . . . የተፈጥሮ ህግ አክብዶ ልብህ ላይ የከተበው እውነት አለቻ …ትዳር አብሮ ጮርናቄ የመብላት አብሮ አልጋ ላይ የመንከባለል ተራ ጥምረት አለመሆኑን ሹክ ይልሃል ! አየህ የአንተ ማንነት ወይም የሚስትህ ምንነት ሳይሆን የቃሉ ህያውነት በጥምረቱ ውስጥ አንዳች ፍርሃትን የሚነዛ ሃይል ይለቅበታል …

አንተ ርኩስ ብትሆን እንኳን (ያልረከሰ ሰው የለም እንጅ) ትዳር ቅዱስ ነው ሲል ነገሩ እዛው ላይ አብቅቷል ! ያንተ ስራ የፈጣሪን የድምፅ ሞገድ የሚያስቀይር ‹‹ሪሞት ኮንትሮል›› አይደለም ! ያ ነው ለሰው ያልገባው …. እዚች ልጅ ጋር ይሄን የመሰለ ልጅ እንዴት በትዳር ቆየ ወይም ውይ ይች መልአክ ልጅ እንዴት እዚህ ጋር አንድ ቤት ኖረች ….የሚል ጥያቄ ….የሰው ማንነት ላይ አይደለም ትዳር የሚመሰረተው አትድከም …እፍ የተባለበት ሃይል አለ ! ህያው የሆነ ቃል ! ለዛ ነው በምድር ታላላቆቹ የሆሊውድ ሰዎች ሳይቀሩ የትዳር ፍቻቸው አለምን የሚሞላ ዜና ሁኖ የሚራገበው !! በየምሽቱ ማንም ጋር ሲጋደሙ ማን ያወራል ቢበዛ ተራ ዜና ነው !


ማርታ ጋር ከተፋታን አመት ሆነን …አልዋሽም አንዳንዴ ትናፍቀኛለች …አለ አይደል በቀጥታ ወደቤቴ ሂጀ እንደድሮው ጉንጯን ስሜ እሽ ውሎ እንዴት ነበር ብየ ምንም እንዳልተፈጠረ ነገሩን ከቆመበት ልጀምረው ያምረኛል ሃሳቡ ራሱ ያረካኛል !ይሄ ሁሉ ለመሳም ተወልውሎ የሚወጣ ጉንጭ የብርጭቆ ወረቀት ነገር ይሆንብኛል ! አንዳንዴ ታዲያ የሚያውቁኝ ሴቶች ጋር እገናኝና ስናወራ …ስናወራ ብቻ አይደለም በተፋታ ሂሳብ መንጎዳጎድም አለ ….‹‹ውይ ይሄኮ ያጋጥማል አትጨናነቅ ባክህ ህይዎት ብዙ አማራጭ አላት ምናምን›› እያሉ ያወለቁትን ቀሚስ ወላ ሱሪ መልሰው እየለበሱ . . . ይሄ ቀሚስ ስንት ቦታ ወልቆ ይሆን እላለሁ ….የአወላለቅና የአለባበስ ፍጥነታቸው አንዳንዴ ልምዳቸውን ይናገር የለ !ደግሞ ተኝተው ከተነሱ በኋላ ፊታቸው ላይ የሆነ ርካታ አለ ‹‹ጣልኩት›› አይነት የድል ፈገግታ ….ሰው አብሮ ወድቆ ሌላውን የጣለ ሲመስለውኮ ነው የምደመመው !


በአይናቸው የተከፈለ ማንነቴን ከራሳቸው የተረገመ ግማሽ ጋር ሊቀላቅሉት ሲቋምጡ እየታዘብኩ እገረማለሁ ! በነገራችን ላይ ታዝቢያለሁ ብዙ ሴቶች ከነመፈጠሩ እንኳን ትዝ የማይላቸው ወንድ ባለትዳር መሆኑን ሲያውቁ የሚያንቀዠቅዣቸው ነገር አለ …!!ትዳር ፈረሰ ሲባል ያልደነገጠች ሴት እንዴት ነው ትዳር ከእርሷ ጋር መመስረት አክብዳ የምታየው …የእህቷ ስጋ ፈራሽ የሷ ዘላለማዊ የፀና ግንብ ነው እንዴ …‹‹እኔ እንደሌሎች ሴቶች አይደለሁም ›› ይባልልኛላ ….ለምን ብትላት ፀጉሬን የምሰራው ውድ ቤት ነው ለማለት ! ፀጉርም መንፈስ ነው ልብስም መንፈስ ነው … ታከብረው ዘንድ የተሰጠህን አንተነት በፍቅርም ስም በለው በምን የጣልከው ቀን ሁሉም መላጣ ነው ! በቃ ትዳር ቦርሳ አንጠልጥሎ የባልን ክንድ ይዞና ቀለበት ሰክቶ ሰበር ሰካ ይመስላቸዋል ….እንዲህና እንዲያ እያሰብኩ አራዳ ህንፃ ላይ ተቀምጨ ቁልቁል አላፊ አግዳሚውን አያለሁ . . .


አራዳ ህንፃ ለምን እንደሆነ እንጃ ህንፃ አይመስለኝም ….መሃል ፒያሳ ቁሞ ጥርሱን የሚፍቅ ጎልማሳ ነው የሚመስለኝ ! ህንፃው የሆነ ሌላ ህንፃ ቀጥሮ የሚጠብቅ ጎልማሳ ….አለ አይደል ሌላ ሴት ህንፃ ምናምን… ምናልባትም ህንፂት የምትባል የመስታዋት ቀሚስ የለበሰች የአሉሚኒየም ብራዝሌት የደረደረች ዘመናዊ ሴት ህንፃ … ህንፃ ነብስ የለውም ያለው ማነው ?…የስንት ወዛደር ደምና ላብ ትንፋሽና ምሬት ከስሚንቶና ብሎኬት ጋር ሰርጎ ሰዋዊ መሻት እፍ ብሎበት ቢሆንስ ….ማንም አያውቅም በተለይ ሰው አላዋቂ ፍጡር ነው ! ፊታችን የቆመውን ሰማኒያ ኪሎ ስጋና አጥንት ባይን ከመመዘን ያለፈ ምን እውቀት አለን ….ቃል አጋጭተን ከጨመቅነው አመክንዮ እውነት ያልነውን ጭማቂ ከመጨለጥና ከማግሳት ያለፈ ምን መገለጥ አለን ….ሰው ነና …ቆይ በደንብ ይጨመቅ አንል ነገር ጥማችን ፋታ አይሰጠንም)

 

ህንፃና ህንፃ ፒያሳ ሲቀጣጠሩ ህንፂት ከወደሜክሲኮ ወላ ከወደሃያሁለትና ቦሌ እየተራመደች ትመጣለች ማለት ነው ? አይደለም! …ግን ፊት ለፊት ያሉ አሮጌ ቤቶችን በአመፀኛ ዳሌዋ ገፋ አድርጋ እነሱ ቦታ ላይ ልክ በቀጠሮ ሰዓቷ ብትበቅልስ … አሁን አራዳ ህንፃ ፊት ለፊት ያሉትን ጭርንቁስ ቤቶች አፈራርሳ አንዲት ሴት ህንፃ ብትቆም ‹‹ታሪክ ተደመሰሰ ›› እንጅ አራዳ ህንፃ ሲጠብቃት የኖረችው ሴት ህንፃ መጣችለት … ብሎ ለህንጻዎች ፍቅር የሚያጨበጭብ ማነው …. እያልኩ ቡና እጠጣለሁ. . . አቤት ቡና ስወድ ! እኔ መቸም ሊገድለኝ የሚፈልግ ጥሩ ጠላት ቢኖረኝ ቡና ውስጥ መርዝ ጨምሮ እንዲሰጠኝ ነበር የምመክረው ! ሞት በምትወደው ነገር ሲገለጥኮ የሆነ ውበት አለው ….ከሞቱ አሟሟቱ ማለትኮ አሟሟት ከሞት እኩል ዋጋ እንዳለው አመላካች ፈሊጥ ነው !

 

መኪናውን… ሰውን … ቁልቁል እያየሁ … ! እዚህ ቦታ ስቀመጥ ሁልጊዜ ቀጠሮ ያለኝ ይመስለኛል …ያልቀጠርኩትን ሰው የምጠብቅ አይነት . . . ለነገሩ ህይወት ከቀጠርነው በላይ ያልቀጠርነው አጋጣሚ ጋር ስታጋጫን ነው ጣእሟ የሚሰማን . . . ድንገት ከፊቴ ካለውና አንድ ጠረጴዛ ከምጋራው የፕላስቲክ ወንበር ኋላ የቆመች አንዲት ምቾት መድረሻ ያሳጣት ሴትዮ‹‹ሰው አለው ?›› አለችኝ ፊት ለፊት ቁጭ አለች … ቁመቷ የትየለሌ …..አለባበሷ የሆነ የማይገልፁት ግን የሚያምር አይነት …ነገረ ስራዋ ሁሉ ረጋ ያለ ነው …


መጀመሪያ ዣንጥላዋን አጠፈችና በስርአት ጠቅልላ የድሮውን ባለስሙኒ ባኒ ዳቦ አሳክላ ቦርሳዋ ውስጥ ከተተቻት …ቀጥላ ጥቁር መነፅረዋን አውልቃ ጠረቤዛውን በሶፍት እንደመወልወል አድርጋ አለመቆሸሹን ካየች በኋላ መነፅሩን የወለወለችው ቦታ ላይ አስቀመጠች … ወደደረቷ ግድም ያለ ልብሷን …ሳብ ሳብ እያደረገች ጡቶቿን እንደመሸፈን ይሁን እንደመግለጥ ባልገባኝ መሽሞንሞን !…. ተለቅ ያለች ሴት ናት ግን ደግሞ ሸንቀጥ ብላ ራሷን ላለፉት አስር አመታት በምግብ …በስፖርት በሳውና ባዝ እና በወዘተ በሚባሉ ስጋዊ ድሎቶች የጠበቀች አይነት ….

ነፋስ ከበስተጀርባዋ ነፈሰ ….ሽቶዋን አምጥቶ አወደኝ …ከዛን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አራዳ ህንፃ ምንምን ይሸታል ቢሉኝ ያንን ያንን ሽቶ እላለሁ !አንድ ሰው ድንገት የዚችን ሴትዮ እድሜ ቢጠየቅ አፉ አምልጦት 30 ካለ በኋላ ቀና ባለ ቁጥር አምስት እየጨመረ አለ አይደል 35 …40 …45… እያለ 50 ድረስ መሄዱ አይቀርም ! 50 ከደረሰ በኋላም እንደገና መመለስና 45 …እያለ መገመቱ አይቀርም አለ ግራ አጋቢ ስጋ !

ይሄን ሁሉ ካደረገች በኋላ አንገቷን ቀና አድርጋ( ቀይ አንገቷ ላይ አግድም አራት የሚሆኑ ወደቡናአይነት የሚያደሉ እድሜ ወለድ መስመሮች አሉ የኮንሶን እርከን የመሳሰሉ ) አይኖቿን ወደሰማይ አንስታ ቁልቁል የተለቀቀ ፀጉሯን አርገፈገፈችና ‹‹ እፎፎፎይይይይ አሉ እተጌ ጣይቱ›› አለች ….ልክ እንዲህ ስትል ፊቷ ላይ ያለው እርግጠኝነት እቴጌ ጣይቱን በቅርበት የምታውቃቸው መስሎ እንዲሰማኝ አደረገኝ ….ያው ንግስቲቱ ፍልውሃ አረፋፍደው ወይ ቤተ ስኪያን ስመው እዛ እንጦጦ ሲመለሱ ‹‹ውይ እትየ መጡ እንዴ ›› እያለች ተቀብላ እግራቸውን ቀዝቃዛ ውሃ በተሞላ የእንጨት ገበቴ ለቅለቅ የምታደርግ እዛ ስታለቀልቅ አንድቀን ‹‹እፎይ›› ሲሉ በጆሮዋ የሰማች የአይን ምስክር መሰለችኝ….የንግስቲቱ አገልጋይ ጋር አንድ ጠረጴዛ የተጋራንም መሰለኝ …!በመምሰል ነው ነገር የሚጀምረው!

እንደውም አፈጠጥክ እንዳልባል በተሸራረፈ ማፍጠጥ አይቸ አእምሮየ ውስጥ ሳገጣጥማት እድሜዋ ወደዛው ግድም የሚደርስ አይነት ትልቅ የማታረጅና የማትሞት ሴትዮ መስላ ታየችኝ … (አእምሮኮ ፊት ከሰጡት ) አይኖቿ ስር ያሉት በእድሜ ያኮፈኮፉ ከዛ ሳውና ባዝና ከዛ ጉድ የስጋ ጦርነት ያመለጡ የእድሜ አሻራዎች ብራና መስለው ትላንቷን ሹክ አሉኝ . . . የሴት ልጅ እድሜ ሃቀኛ ክታቡ ከአይን ስር ያለ ቆዳ ላይ እንደሆነ ያወኩትም ያኔ ነው . . . ሴት ጋር ስናወራ አይን አይናቸውን ስናያቸው ‹‹እፍር ›› አልን የሚሉት በተሽኮረመመ ማቀርቀር እድሜን የመሰዎር ጥበብ እንደሆነ ማን ያውቃል !!

ብዙ ዘፈኖች ስለሴት ልጅ አይን እንጅ ከአይን ስር ስላለው ቆዳ ዘፍነው የማያውቁት ለምንድነው እላለሁ …ምናልባት ቦታው በአማርኛ ስም ስለሌለው ይሆናል … (ማነው የዛን ቦታ ስም የሚያውቅ) ደግሞ ለክፋቱ ይሄ ዘመነ ‹‹ሜካፕ›› ከአይን በላይ ላለው ሽፋሽፍት ‹‹ሻዶ›› ሲያዘጋጅ ከአይን በታች ላለው ክፍል ይሄ ነው የሚባል ሜካፕ እንኳን አለመስራቱ ይገርመኛል ! ኑሮስ እንደሆነ ምን አውቃለሁ ….ሰው አላዋቂ ነው… ይመስለዋል እንጅ ….ያወቀ የመጠቀ!

ሴትዮዋ ድንገት ወደኔ ዞር አለችና ‹‹ውይ ቀይ አበዙበት እንጅ ዲዛየኑ ያምራል›› አለችኝ … ስለምን እንደምታወራ ግራ ገብቶኝ ስደናበር ቀይ ጥፍር ቀለም በተቀባ ጣቷ መንገዱን ተሻግሮ ወደሚገኘው ምንጣፍ መሸጫ እድሜ ጠገብ ቤት ጠቆመችኝ …ቀይ ምንጣፍ አሮጌው የጣውላ በረንዳ ክፈፍ ላይ ተሰቅሏል …ትክ ብየ አየሁት እባብ የሚመስል ጥቁር መስመር የተጠማዘዘበት ቀይ ምንጣፍ …

‹‹እ …አዎ›› አልኩ እንደው አልኩ እንጅ ጥሎብኝ የምንጣፍ ዲዛየን የመጋረጃ ቀለም የሚባል ውበት አይገባኝም !! ሴትዮዋ ዘና ያለች ናት …አስተናጋጇ ፊታችን መጥታ ቆመችና ‹‹ምን ልታዘዝ ›› አለቻት …ወደእኔ ዞር ብላ ቡናቸው እንዴት ነው ›› አለችኝ …አስተናጋጇፊት መጥፎ ነገር ተናግሬ አንድ መተከዣ ካፌየ ጋር ልጠማመድ እንዴ …ምኗን ጠንከኛ ላከብኝ . . . 
‹‹ጥሩ ነው›› አልኩ !
‹‹ቡና ›› ብላ አዘዘች ….ቡና እስከሚመጣ ምንም አላወራንም የሆነ አገሩ የናፈቃት ትመስላለች ዝም ብላ ታያለች አስተያየቷ የሆነ የራበው ሰው ምግብ ሲቀርብ እንስፍስፍ ብሎ የሚያየው አይነት ነው . . . ቡናዋ መጣ ….ቀመስ አደረገችና ቀና ብላ አይታኝ ‹‹ ሰራህልኝ ›› አለችኝ አነጋገሯ የወዳጅነት ነው ! 
‹‹እንዴ አስተናጋጇ ፊት ስትጠይቂኝኮ ….›› 
‹‹ፈገግ አለች …›› ፈገግ ስትል ድዷ ይታያል ጥሎብኝ ሲስቁ ድዳቸው የሚታይ ሰዎች ይሸክኩኛል … የሆነ አላጋጭ ነው የሚመስሉኝ …አለ አይደል ብዙ አመት በማላገጥ ጥርሳቸው እያጠረ እያጠረ ሂዶ ድዳቸውን መጠቀም የጀመሩ !

እንዲህ ነበር የተዋወቅነው አርፌ በተቀመጥኩበት …እጇን ዘርግታ በፈገግታ ስሟን ነገረችኝ ! ጥሩ ትውውቅ ነበር ይሄን ድዷን ብትሸፍንልኝ !!

ይቀጥላል!

Search
Categories
Read More
Uncategorized
አስገራሚ ቃለ ምልልስ -ሙጋቤ
”መቼም ሙጋቤ መልካም ሰው ነው” ይላል- መንግስቱ ሃይለማርያም የክፉ ቀን ደራሹን ማመስገን ሲጀምር።በርግጥ የሙጋቤን መልካምነት...
By binid 2017-11-26 06:36:34 0 0
Uncategorized
ከነጠላው ስር !!
(አሌክስ አብርሃም) የበግ ለምድ የለበሰ ቀበሮ ሁሉ በግ መስሎን ተበላን ጓዶች !!እኛ ኢትዮጲዊያን በተለይ በዚህ ሰአት ‹‹ፈጠራ...
By binid 2017-11-26 06:32:11 0 0
Uncategorized
1964
The chief army commander General Derese Dubale visiting the 4th national first-rank army service....
By Seller 2017-11-14 07:31:18 0 0
Uncategorized
ዳይ እየተሰዳደብን ...
«ዘውድአለም ታደሰ» ሰው ሁሉ የፖለቲካ ተንታኝ ሆኖልኛል። ጭራሽ እየሩሳሌምን ለእስራኤል አሳልፈን አንሰጥም! አንሰጥም!...
By Zewdalem 2017-12-07 12:34:35 0 0
Uncategorized
Ethiopia Travel Guide for Curious Travelers
For those seeking something different, here’s my Ethiopia travel guide that will hopefully...
By binid 2017-11-26 06:56:18 0 0