እስፖርት ጀምረናል

0
0

እስፖርት ጀምረናል!
«ዘውድአለም ታደሰ»

ዛሬ ለምን እንደሁ እንጃ እንቅልፍ አልወስድ ብሎኝ ስገላበጥ አላሁ አክበር አለ! ቢቸግረኝ በስንት ዘመኔ የሰቀልኩትን ቁምጣ አውርጄ ታጠቅሁ ፥ ሸራ ጫማ ፣ ጋምባሌ ፣ ጓንት ፣ የሹራብ ኮፍያ ..... ዎክማኔንም አነሳሁ። ሞቅ ያለ የእንግሊዝኛ ሙዚቃ በመክፈት ጆሮዬ ላይ ሰካሁ! በቃ ትንሽ ወደፊት ቀደም ከሚለው ቦርጬ ውጪ ደምበኛ ስፖርተኛ መስያለሁ! :)

አላማዬ አጭርና ግልፅ ነው! ጠንክሬ በሚቀጥለው ኦሎምፒክ ለዚች ጎድቋላ ሐገር በመቶ ፣ በሁለት መቶ ፣ በአራትና በስምንት መቶ ፣ በሺህ አምስት መቶ ፣ ብቻ በሁሉም ርቀት ተወዳድሬ ወርቅ ማምጣት ነው! በአሎሎ ውርወራም እሳተፋለሁ። ብችል አሎሎውን ከአንዱ ስቴዲየም እስከ አራት ኪሎ እወረውረዋለሁ። ካልተቻለ ግን ለአንድ ሚሊኒየም የማይደፈር ሪከርድ እሰብራለሁ። እንደሚሳካልኝ አልጠራጠርም። “እናቸንፋለን!” ብሏል ሃይሌ!

በሃሳቤ ወርቁን በጠቅላላ ሰብስቤ ወደሃገሬ ስገባ ህዝቡ ሆ ብሎ ወጥቶ ሲቀበለኝ ይታየኛል ... አሁን ጉራቸውን የሚቸረችሩብኝ ቺኮች ሊያስፈርሙኝ ሲራወጡ፣ ሼሁ የወርቅ ክምችቴን አይተው ልጠረው አልጠረው እያሉ ከራሳቸው ጋር ሲወዛገቡ ሃሃ

ብቻ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል! ዛሬ የመጀመሪያዬ ስለሆነ ብዙም መሮጥ የለብኝም። አርባ ሃምሳ ኪሎሜትር ብቻ ዱብ ዱብ ካልኩ ይበቃል። ባይሆን ነገ ወደባህርዳር ሮጥ ብዬ ዘመድ አዝማድ ጠያይቄ ማምሻዬን እመለሳለሁ ... እያልኩ በታላቅ ወኔ ከቤቴ ወጣሁ!

ሩጫ ለኔ አዲስ አይደለም! ብዙ ግዜ ፌደራል አሯሩጦኛል .... እንደውም የሩጫ ታለንቱ እንዳለኝ የገባኝ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አንድ ፌደራል ሲያሯሩጠኝ ነው።
ሰልፉ ሲጀመር ሰላማዊ ነበር። ISIS የተባለው ቡድን ወገኖቻችን ላይ የፈፀመውን ግድያ ለማውገዝ ነበር የወጣነው። በርግጥ ሰልፉን እንዲጠብቁ የተመደቡት ሃይሎች ከሰልፈኛው ቁጥር ይበልጡ ነበር።

ውጪ ሃገር ህዝብ ሰልፍ ሲወጣ የሃገሪቱ ወታደር ሰልፈኛውን ያጅባል። ደከም ላለው ስሎጋኑን ይሸከማል። ውሃ ለጠማው ሃይላንድ ያቀብላል። ፀሃዩ ላንገሸገሸው ዣንጥላ ይመፀውታል።
የኛ ሃገሩ ወታደር ግን ሰልፍ ለማጀብ ሳይሆን ሰልፍ ለመበተን ነው ከቤቱ ሚወጣው! በመጀመሪያ እኔ ነኝ ያለ ቆመጥ ይዞ ሰልፈኛው ላይ ያጉረጠርጣል! ትንሽ ይቆይና ቆመጡን አስቀምጦ መሳሪያውን ያቀባብላል። በመጨረሻው ወደሰልፈኛው ያነጣጥርና ..... (ሞኛችሁን ፈልጉ ማንን ለማስበላት ነው?) የምክር አገልግሎት ይሰጣል :)

ከቤት ወጥቼ በግምት ሁለት መቶ ሜትር የሚሆን እንደሮጥኩ መላ ሰውነቴ ይርገፈገፍ ጀመር! ገና የሰፈሬን የኮብልስቶን መንገድ ሳያልቅ ጉልበቴ ተንቀጠቀጠ ... ምንነቱን ለጊዜው ያልለየሁት ድምፅ ይሰማኛል ..... ወይኔ ዩሴን ቦልት!
በዚህ ሰውነቴ ደፍ ደፍ ስል ያየች ፒንክ የሚሏት የሰፈራችን ነገረኛ ውሻ ጥርሶቿን አሹላ ወደኔ መጣች ... ኡኡ አይባል ነገር እኩለ ለሊት ነው። የቻልኩትን ያክል ሮጥኩ ...ተከተለችኝ .... ሮጥኩ ... ደረሰችብኝ! (አጠገብ ለአጠገብ ስንሮጥ ሃይሌና ፖልቴርጋት ነው ምንመስለው ...) ወይኔ ስንት ኦሎምፒክ ሚጠብቀኝ ሰው የውሻ መኖ ሆኜ ልቅር? ስል እግዜር ይስጣት ውድድር መስሏት ነው መሰለኝ አልፋኝ ሄደች!

ብቻ እንደምንም መስቀል አደባባይ ደረስኩ። እናንተ!! የኢትዮጲያ ህዝብ ግን ሲያሳዝን። አይተኛምኮ! ገና ጨለማው ሳይገፈፍ ቢሆንም የደረስኩት አንድ ሃገር ህዝብ ቀድሞኝ እየተሯሯጠ ጠበቀኝ። ህዝባችን በቃ ይጨነቃል ማለት ነው? እንቅልፍ የለውም ማለት ነው? በዚያ ላይ ክሳታቸው። አንድ ስጋው ሞላ ያለ ስፖርተኛ የለም። ጉንጫቸው የጎረጎደ ስፓይናል ኮርዳቸው በሹራባቸው ስር የሚታይ ፣ የለበሱት ቱታ እንደአብርሃም ድንኳን የሰፋቸው ከሲታ ሰዎች ነው ወዲያ ወዲህ ሚሉት። እውነት ለመናገር ለአብዛኞቹ ሚያስፈልጋቸው ስፖርት ሳይሆን ..... አጥሚት ነበር! አጥሚት ጠጥተው ከዚያ መተኛት! የምን ስፖርት ነው ደግሞ? :)

ልክ ወደስፖርተኞቹ ስቀላቀል ለመጀመሪያ ግዜ ወፈር ያለ ሰው ያዩ ይመስል ቆመው ማንሾካሾክ ጀመሩ ... ወደጥግ ሁለት ረሃብ አድማ ላይ ያሉ የሚመስሉ አትሌቶች የሚነጋገሩት ይሰማኛል
«ይሄ እየተንደባለለ የሚመጣው ሰውዬን እየውማ» ይላል አንዱ ..
«ትራፊክ መሆን አለበት» ይላል ሌላው
«እንደኔ እንደኔ የቦቴ መኪና ሾፌር ነው» ይላል ሌላኛው።
ብቻ እነሱ በኔ ውፍረት ሲገረሙ እኔም በነሱ ክሳት ስደነግጥ ትንሽ ቆይቼ እንደገና ዱብ ዱብ ማለት ጀመርኩ። አቤት እሯሯጥ! ለካ መክሊቴ ሩጫ ነው። “ራሴን ፈልጌ አገኘሁ!” አልኩ ሁለት ዙር እንደዞርኩ።
ሶስተኛው ዙር ላይ ግን እየደከመኝ ፣ እያዞረኝ ፣ እያጥወለወለኝ መጣ! አራተኛው ዙር ላይ ስደርስ ...

ትቀልዳላችሁ እንዴ? አራተኛ ዙር የሚባል የለም ሶስተኛው ዙር ላይ በጀርባዬ ተዘርሪያለሁ! ቢያንስ ለሶስት ሰአታት ተዘርሬ የማለዳዋን ፀሃይ በተኛሁበት ሞቅሁና ትንሽ ብርታቱን ሳገኝ እንደገና መሮጥ ጀመርኩ።

ጥቂት እንደሮጥኩ ጀርባዬን ከበደኝና ፊቴን ወደኋላ ስመልስ አንድ እንደጣውላ የተላገ ኮሳሳ ሰውዬ አሯሯጤን ወዶት ነው መሰለኝ እየተከተለኝ ይሮጣል። ቀዝቀዝ ሳደርገው እሱም ቀዝቀዝ ይላል። ፈጠን ስል እሱም ይፈጥናል ... ብቻ ጥቂት እንደሮጥኩኝ እንደተለመደው ስለደከመኝ ቆምኩ። ሰውየውም ከኔ ፈቀቅ ብሎ ቆመ! ሆሆ ምናባቱ ፈልጎ ነው ይሄ ሰውዬ? እያልኩ ሰውነቴን ሳፍታታ እኔ ማደርገውን እየተከተለ ያደርጋል። ቁጭ ብድግ ስሰራ አብሮኝ ይሰራል። እጄን ሳፍታታ አብሮኝ ያፍታታል። በሁኔታው እየተገረምኩ ፑሽአፕ ልሰራ ዝቅ ስል እሱም ፑሽአፕ ለመስራት ተዘጋጀ። ስጀምር እሱም ጀመረ።
ጥቂት እንደሰራሁ በጣም ደከመኝ። እሱ ግን ያለምንም ድካም አከታተለው። እንደምንም ከሱ ላለማነስ ስሰራ ቆይቼ ቀና ብዬ ሳየው ፑሽአፕ እየሰራ መሆኑን ጭራሽ የረሳው ይመስላል። ተስፋ ቆረጥሁና እዚያው በደረቴ ተኛሁ! በሚገርም ሁኔታ እሱም እስፖርት መስሎት ነው መሰለኝ በደረቱ ተኝቶ አይን አይኔን ያየኝ ጀመር። እኔ ለራሴ ልቤ ልትወጣ ደርሳለች በጭንቀት እጆቼን ሳወናጭፍ እሱም ያወናጭፋል። ኡፍፍፍ ብዬ በሃይለኛው ስተነፍስ እኔን ተከትሎ ይተነፍሳል። በሁኔታው ብበሳጭም መነሳት ስላልቻልኩ እዛችው አይኔን ጨፍኜ ተንጋልዬ ተኛሁ። ሰውየውም አይኑን ጨፍኖ ተኛ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አይኔን ስገልጠው ሰውየው የእውነት እንቅልፍ ወስዶት ያንኮራፋል።

ተነስቼ አይኔን ወዲያ ወዲህ ሳንከራትት ሴቶቹ ላይ አረፈ። አቤትትትት ሴቶች!! አሁን ስፖርት ለመስራት ሜካፕ ተቀብቶ ይወጣል? በዚያ ላይ መቀመጫቸው!! ምን አለፋችሁ ከኋላ ታሪካቸው ይልቅ ኋላቸው የሚያምር ሴቶች ወዲያ ወዲህ ይላሉ። የሆነ ስፖርት እየሰሩ ሳይሆን ፋሽን ሾው እያሳዩ ነው ሚመስሉት። የአንዳንዶቹ መቀመጫ ስፋትማ ያስደነግጣል! የቀድሞ ጠቅላያችን “ሃገራችን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ትሁን” ያሉት ይሄን መቀመጫ አይተው ይሆን እንዴ? የሆነ አነስተኛ ቀበሌ በሉትኮ! አሁን ይሄም መቀመጫ ታክሲ ውስጥ ከኛ እኩል የአንድ ሰው ይከፍላል? እያልኩ ስተክዝ ቆይቼ ወደቤቴ በሩጫ ተመለስኩ።

(በሩጫ የሚለው “በታክሲ” በሚል ተተክቶ ይነበብ)

ፍለጋ
Categories
Read More
Uncategorized
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የተከታታይ ትምህርት መርሃ-ግብሮች ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ተባለ፡፡
ተከታታይ የትምህርት መርሃ-ግብር አያሌ ዜጐችን በማታ፣ በክረምትና በእረፍት ቀናት ተምረው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ማስቻሉ በጥናት...
By Seller 2017-11-15 07:31:38 0 0
Uncategorized
ሀገራዊ ዕብደት
(ዳንኤል ክብረት) ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ በቤታችን ደኅና መጥፋቱ ነወይ የሚል የበገና ዘለሰኛ አለ፡፡ አሁን ያለችውን ሀገራችንን ቀድሞ ያየ...
By binid 2017-11-25 13:24:18 0 0
Uncategorized
የከፍታው ዘመን ተጀመረ! (ሃፒ በርዝ ዴይ)
የከፍታው ዘመን ተጀመረ! (ሃፒ በርዝ ዴይ)፡ፒስ ነው ጋይስ?!ቃሉን የማያጥፈው መንግስታችን "መጪው ዘመን የከፍታ ነው" ባለው መሰረት ከሰሞኑ ዶላሩን...
By andualem 2017-11-12 15:14:07 0 0
Uncategorized
Qo'annaa Macaafa Qulqulluu!
Macaafa qulqulluu beekuu barbaadda??? Macaafni qulqulluun fayyisaa fi bu'uura jireenya Adduunyaati!
By T002 2017-11-17 10:07:23 0 0
Uncategorized
ከቆንጆ ሴቶች ጀርባ
ከቆንጆ ሴቶች ጀርባ ....!«ዘውድአለም ታደሰ» ትናንትም እንደፈረደብኝ አንድ የቀረኝ ጓደኛዬን ድሬ እያጨበጨብኩ ወደቤት ገባሁ! በቃ...
By Zewdalem 2017-11-25 01:12:07 0 0