እንቆቅልሽ የሆነው የወተት ምርት
ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ፣ በዓለም ከ10 አገሮች መካከል አንዷ ብትሆንም ከወተት ሀብቷ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች ስላለመሆኗ ይወሳል፡፡ በሌላ በኩልም ሌላው ዓለም ባለው የእንስሳት ቁጥር ልክ ወተትን በየገበታው በተለያየ መልኩ ሲጠቀም እንደሚታይ በኢትዮጵያ ግን ባሉት እንስሳት ልክ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ አለመሆኑ ይነገራል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዓመታዊ የወተት ምርት ከአራት ሚሊዮን ሊትር የዘለለ አይደለም፡፡ ባንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ ለአንድ ሰው በዓመት በአማካይ የሚደርሰው የወተት መጠን 19 ሊትር ብቻ ሲሆን...